የታይሮይድ እጢና ህመም

የታይሮይድ እጢ፣ እንቅርትና የታይሮይድ ካንሰር ምንድን ናቸው?

ያለግርታ ለመግባባት ያመቸን ዘንድ ከታይሮይድ እጢና ህመም ጋር ተያያዝ የሆኑ ቃላትን ስያሜ ወጥ የሆነ ትርጓሜ መስጠት አስፈላጊ ነው።

የታይሮይድ እጢ (thyroid gland)
የታይሮይድ እጢ በፊት ለፊተኛው የአንገታችን ክፍል ከማንቁርት ግርጌ የሚገኝ ለሰውነታችን በጣም አስፈላጊ ንጥረ ቅመሞችን (ሆርሞን) የሚያመርት የአካል ክፍላችን ነው።
በቅርጹ ቢራቢሮ መሳይ ሲሆን በአማካኝ ክብደቱ ከ20 እስከ 25 ግራም ይመዝናል።
የታይሮይድ ሆርሞን ዋና ዋና ተግባራት
• የሁሉንም የሰውነታችንን ህዋሳት ስራና መስተጋብር (metabolism) ይቆጣጠራል
• የሰውነት ሙቀትን ያስተካክላል
• ስርአተ እንሽርሽሪትንና የምግብ ውህደትን ያቀላጥፋል
• የአካላዊና አእምሮአዊ እድገትን ያሳልጣል

የታይሮይድ ህመም

የታይሮይድ እጢን የሚያጠቁ በርካታ በሽታዎች ያሉ ሲሆን በዋናነት በሶስት ከፍለን ልናያቸው እንችላለን
1. የታይሮይድ ሆርሞን እጥረት
2. የታይሮይድ ሆርሞን መብዛት
3. የታይሮይድ እብጠት (እንቅርት)

 

 

የታይሮይድ እብጠት (እንቅርት, goiter)

 

በአብዛኛዎቻችን ላይ የትይሮይድ እጢ ሊታይ ወይም ሊዳሰስ አይችልም። ይህ እጢ አብጦ በቀላሉ ለመታየት ሲበቃ እንቅርት ይባላል።
እንቅርት የሚለው ቃል ባጠቃላይ የተይሮይድ እጢ መተለቅንና እብጠትን የሚያመለክት የታይሮይድ ህመም አይነት ነው። ቃሉን የምንጠቀምበት የታይሮይድ እጢን በመጠን መግዘፍ ለማሳየት እንጅ የአብጠቱን ምንነት አያመላክትም (ሆርሞን የሚያመነጭ ወይም የማያመነጭ ሊሆን ይችላል፣ ካንሰር የሆነም ይሁን ያልሆነ ሞኝ እባጭ ሁሉ ባንድላይ እንቅርት ሊባል ይችላል)
የእንቅርት አይነቶች ብዙውን ጊዜ በሶስት አይነት ይከፈላሉ
የመጀመርያው አይነት እብጠት ሆርሞን የማያመነጭ ቀላል እንቅርት (simple goiter) ነው።
• የአዮዲን እጥረት ሲኖር፤ ታይሮይዳችን በቂ የሆርሞን ማምረት ሲያቅተው የታይሮድ ህዋሶችን በማተለቅና እንዲያንሰራሩ በማድረግ እጠረቱን ለማካካስ በሚሞክርበት ጊዜ እንቅርት ይከሰታል
• በእርግዝናና ጉርምስና ጊዜ፤ ተጨማሪ ሃይል ስለሚያስፈልግ የተይሮይድ መጠን ስለሚጨምር እንቅርት ይከሰታል
የሁለተኛው አይነት እብጠት ሆርሞን የሚያመነጭ እንቅርት (toxic goiter) ነው።
ሶስተኛውና አይነት አብጠት ደግሞ የታይሮይድ ካንሰር ነው
ካንሰር የሚከሰተው የታይሮይድ ህዋሳት ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ ሲራቡ የሚፈጠር ነው።
የታይሮይድ ካንሰር በቀላሉ ለማየት በሚመች የአንገታችን ክፍል ላይ ስለሚወጣ በቶሎ ሳይሰራጭ ለማከም ይመቻል። በጊዜ ከታከመም በጣም ጥሩ የመዳን እድል ያለው የካንሰር አይነት ነው።

የታይሮይድ ካንሰር ምልክቶች ምንድር ናቸው?

መጀመርያ ላይ ታማሚው ምንም አይነት የህመም ምልክቶች
ላያሳይ ይችላል።
• ከአንገታችን ፊት ለፊት ላይ እብጠት (እንቅርት) መውጣት
• በመተንፈሻና ጉሮሮ ላይ በሚያሳድረው ጫና ምክኛት
ለመተንፈስ መቸገር በተለይ በከርባ ስንተኛ እንዲሁም ምግብ
ለመዋጥ ማስቸገር
• የድምጽ መጎርነን
• የማያቋርጥ ሳል

የታይሮይድ ካንሰርና ካንሰር ያልሆነ እንቅርት እንዴት ይለያል?

• እነኚህን ሁለቱን ካንሰር የሆኑና ያልሆኑ ህመሞች መካከል
ያለውን ልዩነት በሚያሳዩት ምልክቶች ብቻ ለመለየት
አስቸጋሩ ሊሂን ይችላል። ነገር ግን የተወሰኑ ካንሰር አመላካች
ምልክቶች አሉ
• በጥቂት ሳምንታትና ወራት ውስጥ ፈጣን እድገት የሚያሳይ
እብጠት
• መጠኑ በጣም ትልቅ ከሆነ በተለይ ከ4ሳሚ በላይ ከሆነ
• በዙርያው ካሉ የሰውነት ክፍሎቻችን ጋር የተጣበቀ ከሆነ
• እንደ አዲስ የጀመረ ህመም ካመጣ፣ ሳል ወይም ማፈን ካመጣ
• ለጨረር ተጋላጭነት ከነበረ
• በቤተሰብ ካንሰር ካለ

የታይሮይድ ካንሰር ስርጭት በአለማቀፍና በሃገራችን
ያለው ሁኔታ ምን ያክል አሳሳቢ ነው?

የታይሮይድ ካንሰር ብዙ የተለመድ ህመም አይደለም። ባጠቃላይ
ካሉት የካንሰር አይነቶች ውስጥ 1 በመቶ አካባቢ ያክል ይይዛል።
ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ታጋልጭ ናቸው። የእድሜ ተጋላጭነትን
ስንመለከት እድሜ ሲጨምር በታይሮይድ ካንሰር የመያዝ እድልን
የሚጨምር ሲሆን በተለይ ከ40ዎቹ በላይ ያሉትን ያጠቃል።
በሃገራችን ኢትዮጵያ ከ10 እስከ 15 ሺህ ሰዎች በታይሮይድ ካንሰር
ሊጠቁ እንደሚችሉ ይገመታል።

የታይሮይድ ካንሰር ለመለየት የሚደረጉ የህክምና ምርመራዎች ምንድር ናቸው?

በመጀመርያ የጤና ባለሙያው የታካሚውን አንገት በመዳሰስ
እብጠት መኖሩንና መጠኑን ይመረምራል
በመቀጠልም የደም የታይሮይድ ሆርሞን መጠን ምርመራ
ይታዘዛል ፣ ይህም TSH, T4, T3 የሚባሉ የላቦራቶሪ
ምርመራዎች ናቸው
እንዲሁም የታይሮይድ አልትራሳውንድ ይሰራል። ይህም
የእባጩን መጠንና ብዛት ይለካል፣ ውስጡ ያለው ፈሳሽ ነው
ወይስ ጠጣር ነው የሚለውን ያጣራል፣ የካንሰር ጸባይ
ያለቸውን እባጮች ይለያል
ራጅም እንዳስፈላጊነቱ ሊታዘዝ ይችላል፤ በተለይ ወደ ደረት
ውስጥ ያደገ እባጭ ለመለየት ይጠቅማል
ራድዮኢሶቶፕ ስካን ሌላይ የምርመራ አይነት ነው

የታይሮይድ ካንሰር ህክምና ምን ይመስላል?

• የታይሮይድ ቀዶ ህክምና
• የራድዮአክቲቭ አዮዲን ህክምና
• የታይሮክሲን መድሃኒት፤ እባጩ መልሶ እንዳያቆጠቁጥ
ይከላከላል
• ቋሚ የሆነ ክትትል ይፈልጋል

የታይሮይድ ካንሰርን እንዴት መከላከል ይቻላል?

ብዙዎቹ የታይሮይድ ካንሰር ተጠቂዎች ግልጽ የሆነ አጋላጭ
መንስኤ ስለማይኖራቸው አብዛኛውን የታይሮይድ ካንሰር ቀድሞ
መከላከል አይቻልም።
በጣም አዋጭው የመከላከያ ዘዴ የህመሙን ምልክቶች በመረዳት
ቶሎ ብሎ የህክምና እንክብካቤ ማግኘት ነው።
ባጠቃላይ የጤናማ የአኗኗር ስልት መከተል በካንሰር የመያዝ
እድልን ይቀንሳል።
በቤተሰብ የታይሮይድ ካንሰር ያለባቸው ሰዎች አንዳንዴ የጀነቲክ
ምርመራ በማድረግ ተጋላጭነታቸውን ሊለዩና ሊጠነቀቁ ይችላሉ።

የመጨረሻ መልእክት

የታይሮይድ ካንሰር በጊዜ ከተገኘ በቀላሉ ሊፈወስ የሚችል ካንሰር
በመሆኑ አንገት ላይ እብጠት ሲያዩ ቀላል እንቅርት ነው ብለው
ሳይዘናጉ ሳይብስ አስፈላጊዉን ምርመራና ክትትል ማድረግ
አስፈላጊ ነው።